News and Events
ዩኒቨርሳል ኮሚኒቲ ደቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ከአብሮነት ዩኬ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለተፈናቃዮች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ 2025-09-02 14:10:34 |
| ደብረ ብርሃን፤ነሀሴ24/2017 (ደብመኮ):- ድርጅቱ ከአብሮነት ዩኬ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ደብረ ብርሃን ከተማ በሦስት መጠለያ ካምፕ ለተጠለሉ 60 እናት አባት ለሌላቸው ተፈናቃይ ህፃናት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ። ዩኒቨርሳል ኮሚኒቲ ደቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ስራ አስኪያጅ አለማየሁ መንግስቴ(ዶ.ር) እንደገለጹት ድርጅቱ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በባህላዊ ጉዳዮች ላይ ተደራሽ በማድረግ ችግርን፣ መድሎን እና መገለልን በማሶገድ የችግር ፈቺ አካል መሆን እንዲችሉ አቅም መፍጠር የሚል ራዕይ ቀርጾ ከተቋቋመበት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ እየሰራ ያለ ድርጅት መኾኑን አስረድተዋል። ዛሬም ከአብሮነት ዩኬ (Abronet UK) ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እናት እና አባታቸውን በተለያየ ምክንያት ላጡ በቻይና፣ በወይንሸት ካምፕ እና በባቄሎ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ለሚኖሩ እና በከፋ ችግር ዉስጥ ለሚኖሩ 60 ህፃናት 90 ኩንታል የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ድጋፉ በህፃናቱ ሞግዚት በኩል ለእያንዳንዳቸው 150 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት መሰጠቱን ሥራ አስኪያጁ አመልክተው በቀጣይም የድርጅቱ ድጋፍ ቀጣይነት እንዳለው ጠቁመዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የስነ ሕዝብ ባለሙያ አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት በከተማው በሶስት መጠለያ ካምፕ ከ23 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ላላፉት 4 ዓመት በችግር ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በሂደቱ ውስጥ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ መኾኑን አስታውሰዋል። ዛሬም ዩኒቨርሳል ኮሚኒቲ ደቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ከአብሮነት ዩኬ በተገኘ ሃብት ወላጆቻቸውን ላጡ 60 ህፃናት ላደረጉት የምግብ ድጋፍ በተፈናቃዮች እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል። በቀጣይም ተፈናቃዮቹ በቋሚነት እስኪቋቋሙ ድረስ ሌሎች ወገኖችም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ድጋፉን ያስተባበሩት የቻይና፣የወይንሸት እና የባቄሎ ተፈናቃይ ካምፕ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየት ተፈናቃዮች በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ዩኒቨርሳል ኮሚኒቲ ደቨሎፕመንት ከአብሮነት ዩኬ ጋር በመተባበር ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ለወገን ደራሽ ወገን ስለኾነ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል። 150 ኪሎ ግራም በነፍስ ወከፍ የተረከቡት የህፃናቱ ሞግዚቶች አክለው እንደተናገሩት በተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል። |
![]() ![]() ![]() ![]() ![]() ![]() |






